በመገደብ (ዓባይን) ልንሠራ ያሰብነውን ታሪክ ባለመገደብ (ዴሞክራሲን) ታሪክ ሠርተን እናጅበው!!


  • PDF
ታላቁ የሚሌኒየም ግድብን እንገነባለን ብሎ መንግሥት ለሕዝብ ይፋ ሲያደርግና የግንባታውን የመሠረት ድንጋይ ሲያስቀምጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀበለው በደስታና በታላቅ የልማት ተስፋ ነው፡፡ የአንድነት መንፈስም ፈጥሯል፡፡ የተለያየ የፖለቲካ አቋም የነበራቸውና ያላቸውም የስምምነት መንፈስን ያስተጋቡበት ፕሮጀክት ነው፡፡
በኢሕአዴግ ለኢሕአዴግ የሚል ስሜት ቀርቶ፣ በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ በሚል መንፈስ ከተፈጠሩት ሥራዎች ሁሉ፣ በግንባር ቀደምትነት ይህ የሚሌኒየም ግድብ ግንባታ ታላቁ ቦታ ተሰጥቶታል ቢባልም ማጋገነን አይመስለንም፡፡ የቦንድ ግዥ እንቅስቃሴውም ይህንኑ ሐቅ የሚያረጋግጥ ይመስለናል፡፡

በርቱ ተበራቱ፤ እንበርታ እንጠናከር፤ ግድቡንም እውን እናድርግ፡፡ ለዚህ ድጋፍ እንጂ ተቃውሞ የለንም፡፡

የምናነሣው ትልቅ ጥያቄ ግን አለን፡፡ ዓባይን በመገደብ ለመሥራት ያሰብነውን ታሪክ፣ ዴሞክራሲንና ፍትሕን ባለመገደብና በማጠናከር ታሪክ ሠርተን ለምን አናጅበውም? በርግጥም ይቻላል!

አዎን! በታላቁ የሚሌኒየም ግድብ አማካይነት መንግሥት የልማትና የአንድነት ሐውልት ለማቆምና ለትውልድ ለማስተላለፍ ያቀደውና የጀመረውን ያህልም፣ ጠንካራ የዴሞክራሲና የፍትሕ ሐውልት ገንብተንም ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንችላለን፡፡

አገርን ለአደጋ እስካላጋለጠ ድረስ፣ የአገርን ደኅንነትና ሉዓላዊነት እስካከበረ ድረስ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ እስከተከተለ ድረስ፣ የእኔ መብትና ጥቅም ይከበርልኝ ብሎ የሌላውን መብትና ጥቅም እስካልነካ፤ ዴሞክራሲንና ፍትሕን ወደላቀ ደረጃ እናሳድገው እናጠናክረው፡፡

ሕገ መንግሥታችን ለዴሞክራሲና ለፍትሕ የቆመ ነው፡፡ ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ፍትሕ ሊባል የሚችል አንቀጽም ሆነ መንፈስም የለውም፡፡

የሕገ መንግሥቱን ግዴታና መንፈስ ይዘን በተግባር ግን እያዋልነው አይደለም፡፡ ተሸራርፎና ተጣምሞ እየተተገበረ ነውና፡፡

በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 29፣ ስለ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትና ስለፕሬስ ያለ ገደብ፣ ድንበር ሳይወስነው፣ በመገናኛ ብዙኀን፣ በኪነጥበብም ጭምር ሙሉ መብት እንዳለ ይገልጽና፣ በተጨማሪም ይህንኑ በተግባር ላይ ለማዋል በሚደረግ እንቅስቃሴ ዙርያ፣ የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግም ያሰፍርና ሕዝብን እሰይ ያሰኛል፡፡ ወደ ተግባር ሲመጣ ግን፣ የማይጥመንን ሐሳብ የሚገልጽና የሚናገር፣ የሚጽፍም ወዮለት፤ እያለ ሰይፍና ሰንሰለት የሚያወዛውዝ ሹመኛ ግን ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ይስተዋላል፡፡

ሕገ መንግሥታችንም፣ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ሕጎቻችንም፣ የፀረ ሙስና አዋጃችንም ሁሉም እኩል ነው፡፡ ሁሉም መብቱና ክብሩ በሕግ የተጠበቀ ነው፡፡ ሙስና ወንጀል ነው፤ ሰብዓዊ መብት ለሁሉም የተረጋገጠ ነው ይላሉ፡፡ እሰየውም ያሰኛሉ፡፡

ወደ ተግባር እንግባ ሲባል ግን፣ ከእነዚህ የሰብዓዊ መብትና የሕግ መከበር ሕጎች መፈክሮች ጎን ለጎን፣ ‹‹ገንዘብ ሲናገር ፍትሕ ዝም ይላል›› የሚሉ መፈክሮችም እኩል ይታያሉ፡፡ እኩል ይተባበራሉ፡፡ ንጹሕና ሕግ አክባሪ ሆኖ መሥራትና መኖር ለሚፈልግ ዜጋም ሥጋትና ሐዘንን ይፈጥራሉ፡፡

አገርም፣ ሕዝብም፣ መንግሥትም ሕጎቻችንና ፖሊሲዎቻችን ልማትን ይማጠናሉ፡፡ አልሚን እናበረታታለን ይላሉ፤ ድህነትን እናጥፋ ይላሉ፡፡ ወደ ተግባር ሲገባ ግን፣ የምታለማው ጉቦ ከሰጠህ ነው፤ እኔን ካከበርክና ለእኔ ከሰገድክ ነው፤ አክሲዮን ካስገባኸኝ ነው፤ የሚሉ ስውር መመርያዎችና ኬላዎች ይፈጠራሉ፡፡

ቅሬታ ካላችሁ በራችን ክፍት ነው፤ ቅሬታ ካላችሁ ለመስተዳድሩ፣ ለቢሮው አመልክቱ፤ ቅሬታ ካላችሁ ለእንባ ጠባቂ አቅርቡ፤ ቅሬታ ካላችሁ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አቤት በሉ፤ ቅሬታ ማቅረብ መብት ነው፤ ሲባል እሰየው ጎሽ ያሰኝ፣ ያስደስትና በተግባር ሲታይ ግን ከተከፈቱ በሮች ይልቅ የተቆለፉ ልቦችና የተቆለፉ ህሊናዎች ይበዛሉ፡፡ ሕዝብ እናገለግላለን የሚሉ የራዕይ መፈክሮች፣ ሕግን አክብሮ አገልግሎት መስጠት የሚሉ ራዕይና ተልዕኮ በየበሩና በየግድግዳው የለጠፉና የአገልግሎት ያለህ ሲባል ግን፣ ‹‹ከአገልግሎት ውጭ ነው›› ይባላል፡፡

ብቻ ብዙ፣ ብዙ ነገር አለ፡፡ ሕዝብና ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮለት በደስታና በኩራት በአገሩ መኖር ሲገባው፣ መብቱና ክብሩ ተገፍፎ የአገር ፍቅር ብቻ ይዞት በአገር ውስጥ የሚኖር ብዙ ነው፡፡

ይህን ሁሉ መቀየር ይቻላል፤ ይህን ሁሉ ቀይሮና አስወግዶ ሕዝብና መንግሥት እጅና ጓንት ሆኖ፣ ተፋቅሮና ተከባብሮ እንዲኖር ማድረግም ይቻላል፡፡ ነገር ግን ቁርጠኛ ውሳኔ ከመንግሥት ይጠበቃል፤ ይፈለጋልም፡፡

ሕግን አክብር የሚል ውሳኔ፣ ሕግን የጣሰ፣ ከሙስና ውስጥ የተዘፈቀ፣ ሰብዓዊ መብትን የረገጠ፣ ያዳላና በገንዘብ የተገዛ፣ የመንግሥት ሹመኛና ሠራተኛ ተጠያቂ ይሆናል የሚል ቆራጥ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ሕግና ደንብ በሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን የሚቆጣጠር ውሳኔና ተግባርም ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት እንዲህ ካደረገና ቆራጥነትን በተግባር ካሳየ፣ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ይቆማል፡፡ ለታላቁ የሚሌኒየም ግድብ ሥራ እየተነሣሣና እየተባበረ እንዳለ ሁሉ፣ ሕዝብም ለዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ፣ ታሪካዊም ሐውልት ግንባታ አብሮ ይነሣል፡፡ ገንዘብ ማዋጣትና ቦንድ መግዛት ብቻ ሳይሆን፣ ጊዜና ጉልበት፣ ገንዘብና ሕይወት ለመስጠትና ለመሰዋትም ዝግጁ መሆኑን ያሳያል፡፡

ይህ ከተሠራ፣ ይህም ሕልም በተግባር ላይ ከዋለ፣ የልማት ሐውልት ብቻ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ ሐውልትም አብሮ ይገነባል፡፡ ጎን ለጎንም ይቆማል፡፡ ትውልድም ይኮራል፡፡ ዓለምም ያከብረናል፡፡

ስለዚህ. . .  .
ስለዚህ፣ በመገደብ (ዓባይን) ልንሠራ ያሰብነውን ታሪክ፣ ባለመገደብ (ዴሞክራሲንና ፍትሕን) ታሪክ ሠርተን እናጅበው!!